አቶ ቢኒያም ምሩፅ ይፍጠር
የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት

የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት መልዕክት

የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአዲስ መልክ በማደራጀት በ11ዱም ክ/ከተሞች የአትሌቲክስ ክለብና ፕሮጀክት እንዲይዙ ለማድረግ በሰፊው የተሰራ ሲሆን በአንደኛና በሁለተኛ ዲቪዚዮን መካከል ያሉትን ክፍተቶች ለማጥበብና እኩል ተፎካካሪ ለማድረግ እንዲሁም የክለብ አደረጃጀት በአዲስ መልክ እንዲዋቀር መስፈርቶችን በማስቀመጥ ከተማ አስተዳደሩን የሚመጥኑ ክለቦችንና አትሌቶችን ለማብቃት በመስራት ላይ እንገኛለን፡፡ በተጨማሪም በከተማ አስተዳደራችን የአትሌቲክስ ስፖርትን ለማስፋፋትና ለማሳደግ ፌዴሬሽኑ ከስፖርት ቤተሰብ፣ ከባለሀብቶችና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየሰራን ሲሆን በ11ዱም ክ/ከተሞች የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት ስልጠና በመደገፍና በመከታተል እንዲሁም አደረጃጀት የሌላቸው ክ/ከተሞች ኮሚቴ በማደራጀት ለስፖርቱ ትኩረት በመስጠት ክለብ እንዲያቋቁሙ ከክ/ከተሞች ከፍተኛ አመራሮችና የስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊዎች ጋር ውይይቶችን በማድረግ ቅስቀሳ እያደረግን ሲሆን ሌሎች ስፖርቱን የሚደግፉ ድርጅቶች ክለብ በመያዝ ፌዴሬሽኑ በሚያዘጋጀው አመታዊ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ አሁን ያለውን የክለቦች ተሳትፎ ቁጥር ለማሳደግ ጐን ለጐን እየሰራ ይገኛል፡፡

ፌዴሬሽኑ በአሁኑ ሰዓት ምንም ዓይነት የመንግስት በጀት ድጋፍ የማይደረግለት በመሆኑ በቀጣይ ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር በመወያየት ፌዴሬሽኑ ዓመታዊ በጀት እዲደረግለት አጥብቀን የምንሰራ መሆናችን ላረጋግጥ እወዳለሁ፡፡

ላለፉት 24 ዓመታት በስፖንሰርነት እንዲሁም ከምንም በላይ የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ለማሳደግ የጀርባ አጥንት በመሆን የሁልጊዜ አጋራችን የሆነው የሞሐ ለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር የፌዴሬሽኑ ህልውና በመሆን ውድድሮችን በየአመቱ እንድናደርግና የቢሮ ሰራተኞችን መቅጠር እንዲቻል ስራዎች በአግባቡ እንዲሰሩና የሙያ ማሻሻያ፣ የአሰልጣኝነትና የዳኝነት ስልጠና በመስጠት ፌዴሬሽኑ የተሻለ አደረጃጀት እንዲኖረው ከማድረጉም በላይ የነበረን ቢሮ አመቺ ባለመሆኑ ቢሮ በመከራየትና አስፈላጊውን የቢሮ ቁሳቁሶች በማሟላት ለስፖርት ቤተሰቡ አስፈላጊውን አገልግሎት እንድንሰጥ ላደረጉልን እገዛ በመላው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪና በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ስም ከፍ ያለ ምስጋናዬን ማቅረብ እወዳለሁ፡፡

የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እስካሁን ያከናወናቸው ተግባራት እና የሚሰጣቸው አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ አልነበረም ይህን ለማሳካት ለመላው ስፖርት ወዳድ የከተማችን ነዋሪዎች የሚሰጡት አገልግሎቶች ለማሳወቅ ይህን ድህረ-ገጽ የከፈትን ሲሆን ያላችሁን አስተያየትና ድጋፍ ለአትሌቲክስ እድገት ሁሉም ባለድርሻ አካል የስፖርት ቤተሰብ፣ የመንግስት ተቋማት፣ የግል ድርጅቶች፣ ባለሀብቶች፣ በተለይም የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽንና የከንቲባ ቢሮ የራሳችሁን አስተዋጽኦ እንድታደርጉ አሳስባለሁ፡፡

አቶ ቢኒያም ምሩፅ ይፍጠር
የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት